የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ የአርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ሚኒስቴርን የሁለተኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።ጿል፡፡
ሚኒስቴሩ ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው በአፋር፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች አርብቶ አደር አካባቢዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ግብዓቶች ተሟልተው ትምህርት ተጀምሯል ብሏል።
በክልሎቹ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች የተገነቡ ሲሆን የመምህራን እጥረት ችግርን ለማቃለልም በጎ ፈቃደኛ መምህራን እየተሳተፉ ነው።
ይሁን እንጂ በአካባቢዎቹ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በአማካይ 30 በመቶ ያህሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አልተመለሱም ነው የተባለው።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ እንደሚሉት፤ በሕዝብ ንቅናቄ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ከክልሎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር መጀመር እንዳለበት ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት በአፋጣኝ ተገልጾ የ9ኛ ክፍል ትምህርት መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመግባቱ በፊት ትምህርት ሚኒስቴር 26 ሚሊዮን ያህል ተማሪዎችን ሲያስተምር ቢቆይም ዘንድሮ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው እንዳልተመለሱ ተገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።