የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ለማካተትና ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ተፈራርመዋል።
የስምምነት ሰነዱ የሰብዓዊ መብቶችን ወደ ማህበረሰቡ ከማስረፅ አኳያ ተደራሽነትን በመጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ተብሏል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ሰብዓዊ መብቶች ሲከበሩ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም መብትና ግዴታውን መለየት የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር ይገባል ብለዋል። በዚህም ረገድ ስምምነቱ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ስልጠና ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ለመሥጠት እንደሚሠራ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል ።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትን በመደበኛው ትምህርት እንደ ግብረ- ገብ እና ዜግነት ትምህርት ውስጥ ትርጉም ባለው መልኩ በማካተት እንዲሠጥ ይደረጋልም ተብሏል።
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ስምምነቱ በኢትዮጲያ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን ከማስፋፋት አንፃር ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለሀገራችን ፈተና ሆኖ ቆይቷል ያሉት ኮሚሽነሩ ይህንንም ለመግታት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የምንሰራው ስራ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም የሙያ እገዛ ከመሥጠት ጀምሮ የተለያዪ ድጋፎችን እንደሚያደርግ በስምምነቱ ተገልጿል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮን ጨምሮ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እንዲሁም የሁለቱም ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዛሬው እለት የተከናወነው ስምምነት ትምህርት ለዘላቂ ልማትና ለዓለም አቀፉዊ ዜግነት የሚለው ግብ ለማሳካት ያግዛል ተብሏል።