1. የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ክልላዊ ፈተናን ለመፈተን በምዝገባ ጊዜ ቀርቦ ያልተመዘገበ/ች ተማሪ ፈተናውን እንዲወስዱ/ድትወስድ አይፈቀድለትም/ላትም፡፡
2. ለ8ኛ ከፍል ክልላዊ ፈተና በመደበኛ ፕሮግራም ተመዝግቦ በፈተና ወቅት ቀርቦ ሳይፈተን ለቀረ ወይም እየተፈተነ እያለ በከፊል የተወ ተማሪ በሚቀጥለው ዓመት በመደበኛ ፕሮግራም ተምሮ ፈተና እንዲፈተን ከሚፈቀድለት በስተቀር ልዩ ፈተና ተዘጋጅቶ አይሰጠውም፡፡ ሆኖም አብዛኛውን ፈተና ተፈትኖ በችግር ምክንያት አንድ ፈተና ሳይፈተን የቀረ ተማሪ ችግሩ በተጨባጭ መረጃ ተደግፎ ሲቀርብ የሠራበት ፈተና ውጤት በ8 የትምህርት ዓይነቶች ተካፍሎ አማካይ ጥሬ ማርክና ፐርሰንታይል ይወጣለታል፡፡
3. ማየት የተሳናቸው ተፈታኞች ሂሳብ፣ ፊዚክስና ኬሚስትሪ ትምህርቶችን እንዲፈተኑ አይገደዱም፡፡ ውጤቱም ከሦስት የትምህርት ዓይነቶች ውጪ ላሉ ትምህርት ዓይነቶች ተካፍሎ ይቀመጣል፡፡
4. ማንኛውም ተፈታኝ በመፈተን ላይ እያለ ፈተናውን እንዳይሠራ የሚያውኩ ሁኔታዎች ቢያጋጥመው በፈታኙ ሲፈቀድለት ችግሩን በመግለጽ አስፈላጊውን እርዳታ ማግኘት ይችላል። ይሁንና በማንኛውም ምክንያት ለባከነ ጊዜ ተጨማሪ ሰዓት አይፈቀድም።
5. ማንኛውም ተፈታኝ ፈተናው ከሚጀመርበት ጊዜ ተኩል ሰዓት /30 ደቂቃ/ ቀደም ብሎ/ብላ ከመፈተኛው ቦታ በመገኘት የፈተና መቀመጫቸዉን መያዝ አለባቸው። ፈተናው ከተጀመረ ከ15 ደቂቃ በኋላ የሚመጣ ተፈታኝ ወደ ፈተናው አዳራሽ መግባት አይፈቀድለትም።
6. ማንኛውም ተፈታኝ ፈተናው ተጀምሮ 45 ደቂቃ ሳይሞላ ፈተናውን ሠርቶ ቢያጠናቅቅም እንዲወጣ አይፈቀድለትም/ላትም። ይሁን እንጂ ፈተናው ከተጀመረ ከ45 ደቂቃ በኋላ ከፈተና አዳራሹ ለመውጣት እንዲፈቀድለት/ላት ሲጠይቅ የመልስ ወረቀቱን ለፈታኙ አስረክቦ/ባ በጸጥታ እንዲወጣ ይፈቀድለታል/ላታል።
7. ፈተናው ሊጠናቀቅ ከ15 ደቂቃ ያነሰ ጊዜ ሲቀረው የሚጨርስ ተፈታኝ የሁሉም ተፈታኞች የመልስ ወረቀቶች እስኪሰበሰቡና ለፈተናው የተፈቀደው የጊዜ ገደብ አብቅቶ እስኪደወል ድረስ በቦታው ተቀምጦ እንዲቆይ ይደረጋል።