የዐሥር ዓመት ታዳጊ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ሶልያና ግዛው አፍሪካን ኮድ (Afri CAN Code) በተሰኘው ውድድር የ2020 አሸናፊ ሆናለች።
ሶልያና በዚህ ውድድር አሸናፊ የሆነችበት ማትስቴይንመንት (Mathstainement) የተሰኘ ፕሮጀክት መሆኑን አፍሪካ ኮድ ዊክ (Africa Code Week) ገልጿል።
ይህ ፕሮጀክት የሞባይል አፕሊኬሽን ሲሆን መሠረታዊ የሒሳብ ዕውቀቶችን ቀላል፣ መካከለኛ እና ከባድ በሚል ደረጃ የከፈለ እና ታዳጊዎች እየተዝናኑ የሒሳብ ዕውቀት የሚገበዩበት ብቻ ሳይሆን ስለ ኮሮና ቫይረስ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑ ልዩ ያደረገው እና ታዳጊዋን ተወዳዳሪ ለአሸናፊነት አብቅቷቷል ተብሏል።
በዚህ ኢትዮጵያዊቷ ታዳጊ ሶልያና አሸናፊ በሆነችበት ውድድር የመጀመሪያዎቹ 10 ተወዳዳሪዎች እና ሀገሮች ይፋ የተደረጉ ሲሆን፣ ሶልያናን ተከትለው የደቡብ አፍሪካ እና የአልጄሪያ ታዳጊዎች የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ ማግኘታቸውን ገልጿል።