የጤና ሚኒስቴር ትምህርት ለመጀመር የሚስችል ሁኔታ መኖሩን ሲያረጋጥልን ትምህርት እንጀምራለን፡- የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.)፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ያለበት ደረጃ ተገምግሞ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን የጤና ሚኒስቴር ማረጋግጫ ሲሰጥና መንግስት ውሳኔ ሲያሳልፍ ትምህርት እንደሚጀመር የትምህርት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ ህፃናት በከፍትኛ ሁኔታ እየተጎዱ በመሆኑ ለእነሱ ቅድሚያ እንደሚሰጥም ነው ያብራሩት፡፡
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ለ6 ወር ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ህፃናት ከዚያ በፊት ለሁለት አመታት ያክል ይዘውት የነበረውን እውቀት ሊያሳጣቸው ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ለህፃናት ቅድሚያ ለመስጠት እቅድ ተይዟል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየውም ህፃናት በኮሮና ቫይረስ የመያዝና የማስተላለፍ ባህሪያቸው ከሌሎቹ የቀነሰ በመሆኑ ድርጅቱ የሚያስቀምጣቸውን የቫይረሱን መከላከያ መንገዶች ሙሉ ለሙ በመተግበር ትምህርት ለመጀመር ጥረት ይደረጋል፡፡
በትምህርት አከፋፈት ዙሪያ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋባቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ትምህርት በ3 ፈረቃ ለመጀመር እቅድ ተይዟል፡፡
ከትላልቅ ከተሞች እርቀው የሚገኙና የቫይረሱ ስርጭት ስጋት በሌለባቸው አካባቢዎችም የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንግዶችን በመተግብር ትምህርት እንደሚጀመር የትምህርት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡