የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ሙያውን አክብረው የሚሰሩ የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሁሉ ትምህርትን እንደ ሸቀጥ የሚቆጥሩ የግል ትምህርት ቤቶችም አጋጥመውናል ብለዋል።
መንግስት የወሰነውን የነፃ ዝውውር ወደ ጎን በመተው የትምህርት ክፍያ ካልከፈላችሁ ወደ ቀጣዩ ክፍል አትዛወሩም የሚሉ የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ አጋጥሞናል ነው ያሉት።
ትምህርት ቤቶች ቀድመው ሲያስከፈሉ ከነበረው የአከፋፈል ስርዓት ውጪ አዲስ የአካፋፈል ስርዓት ሲከተሉ የተገኙ እንዳሉም አንስተዋል።
በዚህ ተግባር ውስጥ የተገኙ ትምህርት ቤቶች እስከ መዘጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።
የትምህርት ቤቶቹ አስተዳደሮች ቢወስኑ እንኳ የተማሪ ወላጆች ማህበር ያልተስማማበት ክፍያም ሆነ አከፋፈል ተቀባይነት የለውም።
አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ የወላጅ ማህበር አባላትን ልጆቻችሁን እናባርራለን የሚል ማስፈራሪያም እያደረሱባቸው ስለመሆኑ ተሰምቷል።
የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርትን እንደ ሸቀጥና ንግድ ከመቁጠር ይልቅ ዜጋን እንደሚያፈራ ተቋም ራሳቸውን ማየትና ለትምህርት ጥራት መጨነቅ ይኖርባቸዋል ተብሏል።
ምንጭ፡- ትምህርት ሚኒስቴር