የመማር ማስተማሩም ሂደቱ የትምህርት ቤት ማህበረሰቡን ደህንነትና ጤንነት ባስጠበቀ መልኩም እንዲሆን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችንም ትምህርት ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላትም እያካሄዱ ነው።
ከነዚህም መካከል በመላ አገሪቱ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁስን ማቅረብም አንዱ እንደሆነም የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሚዩኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሐረግ ማሞ ለቢቢሲ እንደገለፁት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ሙቀት መለኪያ፣ እና የንጽህና መጠበቂያ በአገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሚኒስቴሩ በኦንላይን (በበይነ መረብ) እንደሚሰጥም ገልጿል።
በአገሪቷ ካለው የኢንተርኔት ስርጭት ማነስና የአቅርቦቱ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ጥያቄ ቢነሳም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መመረጣቸውን ኃላፊዋ ገልፀዋል። ከኢንተርኔት መቆራረጥ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችንም ለመቅረፍ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
በቴክኖሎጂ በኩል የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመስጠት ችግር ያጋጥመናል ብለው እንደማያስቡ የሚናገሩት ሐረግ ከኢንተርኔት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየሰራ ነው ብለዋል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ዝግጅት ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንገዶች እገዛ ያገኙ የነበሩ ተማሪዎች ነበሩ። እነርሱስ እንዴት ይታዩ ይሆን ብሎ ቢቢሲ ጥያቄ አቅርቧል።