የትምህርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በጋራ በመሆን የመምህራን ቀን አከባበር ላይ ለሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ገረመው ሁሉቃ (ዶ/ር) መምህራን ትውልድን በመቅረፅ ውስጥ ትልቅ ሚና ስላላቸው ለመምህራን አስፈላጊውን እውቅና እና ክብር መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ መንግስትም ከዘንድሮ ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመምህራን ቀን እንዲከበር መወሰኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮውን የመምህራን ቀን ለየት የሚያደርገው ከዚህ ቀደም በመምህራን ማህበር የሚከበረውን ይህን ቀን መንግስት ሃላፊነቱን ወስዶ ለማክበር በመዘጋጀቱ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ቀኑንም መምህራንን በማክበር፣ በማሰብ እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ጹሁፎችን በማቅረብ እና የፓናልውይይት በማድረግ ታስቦ እንደሚውል ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዮሃንስ በንቲ(ዶ/ር) በበኩላቸው ቀኑን ከማክበር ባሻገር ቀድሞ የነበረውን የመምህራንን ክብር እና ጥያቄ ለመመለስ ይሰራል ብለዋል፡፡
የመምህራን ቀኑም ከመስከረም 20 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል ወጥነት ባለው መልኩ ከትምህርት ቤት እስከ ሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበር ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከ 600ሺህ በላይ የመምህራን አባላት አሉት፡፡